ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በእውቀትና በክህሎት ብቁ አመራሮችን እና ባለሙያዎችን ለማፍራት አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር)
የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር
በብልፅግና ፓርቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ለፓርቲው የኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግኑኝነት አመራሮች እና ባለሞያዎች "የድህረ እውነት ዘመንን በእውቀት እና በእውነት" መሪ ቃል የተዘጋጀው ስልጠና በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ዘርፍ ስር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት የሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አንቂዎች "የድህረ እውነት ዘመንን በእውቀት እና በእውነት" በሚል ርዕስ የአቅም ግንባታ ስልጠና መውሰድ ጀምረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅ/ቤት የህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የሀገራችንን የለውጥ ጉዞ ለማጠናከር እና የህዝባችንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ዘመኑን የዋጀ ፣ የድህረ እውነት ዘመንን የሚመጥን እውቀትና ክህሎት በመያዝ ሀሰተኛ መረጃዎችን መመከትና እውነተኛ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ዘመኑ ሀሰተኛና ስሜት ቀስቃሽ መረጃዎች የሚለቀቁበት የመረጃ ፣ የውሳኔ እንዲሁም የእውቀት ግራ መጋባት የሚስተዋልበት የድህረ እውነት ዘመን መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በእውቀትና በክህሎት ብቁ አመራሮችን እና ባለሙያዎችን ለማፍራት አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዚሁ ወቅት የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ እንደተናገሩት ዘመኑ መረጃዎች በቴክኖሎጂ ተቀምመው እውነቱንና ሀሰቱን ለመለየት አስቸጋሪ በሚሆን አግባብ የሚሰራጩበት የድህረ እውነት ዘመን መሆኑን በአግባቡ በመረዳት ይሄን የሚመጥን ዝግጁነትን መላበስ ይገባል ብለዋል ።
ብልፅግና ፓርቲ ሀገር በቀል በሆነ የመደመር እሳቤ
የሀገራችን ትርክት በቅጡ ተረድቶ ፣ ለሀገራችን የሚበጀውን የብሔራዊነት አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት እየተረባረበ እንደሚገኝ ያወሱት አቶ ሞገስ ይህንን ሀቅ በእውቀት እና በክህሎት ማሳወቅ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት አመራሩና ባለሙያው ሁሌም ለአዳዲስ እውቀቶች እራስን ክፍት ማድረግ እንደሚገባ ያስረዱት ኃላፊው በዛሬው ዕለት መሰጠት የጀመረው ስልጠናም ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ስልጠናው በሁሉም ክልሎችና እና በ2 ከተማ አስተዳደሮች “የድህረ እውነት ዘመን በእውነት እና በእውቀት” በሚል መሪ ቃል ይቀጥላል።