በመጀመሪያው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች በውጤታማነት ተከናውነዋል- ክቡር አቶ አደም ፋራህ
በመጀመሪያው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች በውጤታማነት ተከናውነዋል- ክቡር አቶ አደም ፋራህ
በመጀመሪያው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች በውጤታማነት መከናወናቸውን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች እና በልዩ ልዩ የፓርቲ አጀንዳዎች ላይ ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፤ በመጀመሪያው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች ለህዝብ ቃል የተገቡ ስራዎች በውጤታማነት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ስራን ማጎልበት በወቅቱ አቅጣጫ ከተቀመጠላቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን አንስተው ከዚህ አኳያ የፓርቲውን ተቋማዊ አቅም የሚያጎለብቱ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
የአመራር አቅም ግንባታ ስራ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ መሰጠቱን ገልጸው፤ ይህም አመራሩ በብቃትና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለህዝብ የተገቡ ቃሎች እንዲፈጸሙ ማስቻሉን አንስተዋል።
ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ሌላኛው የጉባኤው አጀንዳ እንደነበር አንስተው በዚህ ረገድ በተለይም በአሰባሳቢ ትርክት ዙሪያ በስፋት በመሰራቱ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልፀዋል።
ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓት ማጠናከር የሚያስችሉ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን አንስተው ይህም ለሀገራዊ አንድነት አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል ነው ያሉት።
የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራትም በስፋት ተከናውነው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ጤናማ የሆነ ትብብርን መሰረት ያደረገ ግንኙነት መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።
ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትም ችግራቸውን በንግግርና በውይይት እንዲፈቱ ምቹ ምህዳር መፈጠሩን ጠቅሰው ለአብነትም የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተከናወኑ ስራዎችን ዘርዝረዋል።
በቀጣይነትም ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ፣ አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ሀገር መገንባት፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው አምስት ቀዳሚ ሀገራት አንዷ እድትሆን ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ ባለፉት አመታት በተሰራው ስራ ኢኮኖሚው በአማካይ በ7 ነጥብ 2 በመቶ እያደገ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው አምስት ሀገራት መካከል አንዷ እድትሆን የተያዘውን ግብ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደረግ ረገድ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ በመቻሉ ከውጭ ይገባ የነበረን የስንዴ ምርት በማስቀረት ወደ ውጭ መላክ የተቻለበትን ታሪካዊ አጋጣሚም ጠቅሰዋል።
የተጀመረው ጥረትም የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥና ከተረጂነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት ጥሩ መሰረት ያኖረ መሆኑን ተናግረዋል።
በዲፕሎማሲ ረገድም ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም በተግባር የሚያስጠብቁ የተለያዩ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በመጀመሪያው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎች፣ የተቀመጡ አቅጣጫዎችና ለህዝብ ቃል የተገቡ ስራዎች ውጤታማ በማድረግ ረገድ ህዝብን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ሚና ከፍተኛ እንደነበር በመግለፅ ምስጋና አቅርበዋል።