የፓርቲው ዓርማና ትርጉም
የፓርቲው ዓርማ
1. የዓርማው ቀለምና አቀማመጥ
በክብ ነጭ መደብ ውስጥ በስተግርጌ ጥቁር ቀለም ያላቸው ለማቀፍ የተዘጋጁ ሁለት የሰው እጅ ምስሎች ያሉት ሲሆን፣ መሐል ላይ ለማቀፍ የተዘጋጁ የሰው እጆች ምስሉ ውስጥ ሆነው የሚታዩ ሦስት የተለያዩ ቀለማት ያላቸው ሦስት ሰዎች የሚገኙበት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከውስጥ ወደ ውጭ የሚፈነጥቁ ቢጫ ቀለም ያላቸው የብርሃን ፍንጣቂዎችን በውስጡ አካቶ ያያዘ ነው።
2. ጥቅል ትርጉም
* ዓርማው የሀገራችንን ኅብረ ብሔራዊነትን፣ ሀገራዊ አንድነትን፣ ብሔራዊ ኩራት፣ ሰላምን፣ ዴሞክራሲንና የብልጽግናን አስተሳሰብ የያዘ ሆኖ ከውስጥ ወደ ውጭ እየሰፋ የሚሄድ የቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትሥሥሮችን የሚያመላክት ነው።
3. ዝርዝር ትርጉም
እጅ፡-
በዓርማው(ሎጎው) በስተግርጌ በኩል የተቀመጠው የሰው የእጅ ምስል ብልጽግና ሁሉን አቃፊ መሆኑን የሚወክል ሲሆን ቀለሙ ጥቁር የሆነበት ምክንያት ኢትዮጵያውያን የጥቁር ሕዝቦች የነጻነትና የድል ተምሳሌት መሆናችንን የሚወክል ነው።
የሰዎች ምስል፡-
ብልጽግና ሰው ተኮር ፓርቲ መሆኑን የሚወክል ሲሆን ፓርቲው ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚታገል መሆኑን ይወክላል። የሰዎቹ ምስል ቀለማቸው ሰማያዊ፣ ቢጫና ሮዝ ሆኖ የተለያየ መሆኑ የኢትዮጵያን ብዝኃነት እንዲያሳይና ብዝኃነታችን የውበታችንና የጠንካራ አንድነታችን ምልክት ሆኖ ተወክሏል።
ጎህ፡-
ከላይ የተቀመጡት የብርሃን ፍንጣቂዎች ጎህን የሚወክሉ ሲሆን ጎህ ጨለማን ሰንጥቆ የሚመጣ ብርሃን እንደመሆኑ መጠን ብልጽግና ኢትዮጵያን ወደ ከፍታና የብርሃን ዘመን ለማሸጋገር የሚታገል ፓርቲ መሆኑን የሚወክል ነው። (የተስፋና የብልጽግና ዘመንን ይወክላል)