ከብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅ/ቤት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን በዛሬው እለት የ79 ዓመት ወጣት የሆነውን ጉምቱውን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጎብኝተናል።
እኤአ ከ1946 ጀምሮ በአንዲት አውሮፕላን ወደ ካይሮ በረራውን የጀመረው የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኩራት የሆነው አየር መንገዳችን በውጣ ውረዶች ሳይበገር በፈተናዎች ተሰናክሎ ሳይቆም ተቋማዊ አቅሙን እያጠናከረ መጥቷል።
አየር መንገዳችን ለነፃና ብቃት ያለው ተቋም ግንባታ ሁነኛ ምሳሌ የሚሆን የፈጠራ፣ የስልጠና ብቃት፣ የባለቤትነት ስሜት፣ የአመራር መተካካትና የቡድን ስራ ውጤታማነት እና የተቋማዊ ነፃነት አሻራ ሆኖ ህያው ብሔራዊ ቅርስነቱን እንዳስጠበቀ ቀጥሏል።
የክብር አርማችንን ከፍ አድርጎ በማውለብለብ ኢትዮጵያን ለዓለም በማስተዋወቅና ሁለንተናዊ እድገቷን በመደገፍ ግንባር ቀደም የሆነውና የእኛ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንም የኩራት ምልክት የሆነው አየር መንገዳችን በአውሮፕላን ደህንነት እና በረራ፣ በመስተንግዶ፣ በካርጎ አገልግሎት፣ በባለሙያዎች ስልጠና እንዲሁም በጥገና እና በሌሎች ተዛማጅ ዘርፎች ያካበተው ልምድ እጅግ አስደናቂ ነው።
በቀጣይም ተቋሙ የጀመረው ጉዞ በስኬት እና በተደራራቢ ድሎች እያሸበረቀ እንዲሄድ ያለንን ልባዊ ምኞት የላቀ መሆኑን እየገለፅኩ ተቋማዊ ጥንካሬውና ብቃቱ ለሌሎች የሀገራችን ተቋማት ልምድ መቅሰሚያ እና የክህሎት መሸጋገሪያ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል በጥንካሬ መገስገሱን እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት አለኝ።
እንደ ብልፅግና ፓርቲም የውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ሀብት የሆነው አየር መንገዳችን ነፃ፣ ገለልተኛ እና ፕሮፌሽናል የሆነ ተቋምነቱን አስጠብቆ በውጤታማነት እንዲቀጥል የሚጠበቅብንን የመንግስት መሪነት ሚና መወጣታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።